Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 10

 

መጀመሪያ ወደ ኮሙኒስቶች መጡ፤ ኮሙኒስት ስላልነበርኩ ምንም አልተናገርኩም፤ ቀጥሎም በሠራተኛ ማኅበር አባላት ላይ ዘመቱ፤ የሠራተኛ ማኅበር አባል ባለመሆኔ ምንም አልተናገርኩም፤ ከዚያም በአይሁዶች ላይ ተነሱባቸው፤ አይሁድ ስላልነበርኩ ምንም አልተናገርኩም፤ በመጨረሻ ላይ ግን እኔው ላይ መጡብኝ፤ የዚያን ጊዜ ግን ስለእኔ የሚሟገት ማንም አልተረፈም ነበር፡፡” Martin Niemöller

ውድ ኢትዮጵያዊ ሆይ ህወሃት/ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር ያለው ትስስር እየከሰመ በመምጣቱ አገዛዙ የሚፈጽመው ድርጊት በሙሉ ማስረጃ አልባ እየሆነ መጥቷል፡፡ በመሆኑም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚካሄደው የተቃውሞ ትግል እና ስልት በህዝቡ ውስጥ በሚገባ በመስረጹና ከህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ ተሰውሮ በተደራጀ ሁኔታ በመመራቱ ከህዝብ ተነጥሎ በመረጃ ዕጦት ብቻውን የሚባትተውን የህወሃት የደኅንነት ቡድን በተፈበረከ መረጃ የዕብደት ክስ ለመመስረት እንዲገደድ አድርጎታል፡፡ ይህም ድርጊቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ መሳቂያ መሳለቂያ እንዲሆን ከማድረጉ ባሻገር ትግሉ ከዕለት ዕለት እየጋመና የድል ብስራትን እየነገረ እንዲቀጥል ካስቻሉ በርካታ ምክንያቶች በዋቢነት ተጠቃሽ ነው፡፡

በህዝቡ ውስጥ ያለው ወኔና ሞራል የፀረ-ወያኔ ትግሉን መስመር እያጠራና እያስተባበረ በመሆኑ ህወሃት ተሸብሯል፤ የኢህአዴግም ሰፈር ተናውጧል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የነፃነት ጎህ ሊፈነጥቅ መቃረቡ የአገዛዙ ድርጊት በራሱ ማስረጃ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው ህወሃት/ኢህአዴግ የነፃነቱን ትግል የሚመሩ አንፀባራቂ ኮከቦችን ሊያጠፋቸው በዕውር ድንብር የሚዳክረው፡፡ እነዚህ ኮከቦች ግን ብቻቸውን አይደሉም፡፡ ከኋላቸው ያስከተሉት ህቡዕና ይፋ የወጡ ኮከቦች በብዛት እንዳሉ ህወሃት/ኢህአዴግ ተረድቷል፡፡ ለዚህም ነው የፍርሃት ዜማውን የሚያላዝነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህዝብና በትግል ኃይሎቹ መካከል የተቋጠረው የፀረ-ወያኔ ትግል ቋጠሮ የት ጋር እንደሆነ ስለተሰወረበት ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ ወዲህ ለህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት የምህረት ልብ የለውም፡፡ በህቡዕ የሚካሄደውን ህዝባዊና ስር የሰደደ የትግል ስልትና አደረጃጀት ሊደርስበት አይችልም፡፡ አባላቱ ተሸርሽረዋል፤ ልባቸውም ከድቷል፡፡ ይህ የደወል መልዕክት ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ በካብ ላይ የቆመ ዛኒጋባ ሆኗል፤ መሠረቱም የአሸዋ፡፡ ከዘር ማጥፋት ጀምሮ በተለያዩ ወንጀሎች በማስረጃ ተጠያቂ የሆኑት አቶ መለስና ተባባሪዎች ብቻ በጣዕር በመንፈራገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ልጆቻቸውም የወላጆቻቸውን ውርደትና ግፍ ስላስነወራቸው በውጭ አገራት ጥገኝነት እየጠየቁ በመለየት ላይ ሲሆኑ የእነዚህን ፈለግ ለመከተል ያኮበኮቡትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ከአንዳንድ ዘረኛ የጦር መኮንኖች በስተቀር አብዛኛው የሠራዊቱ አባላት ልባቸው ሸፍቶ የህዝቡን ትግል እየደገፉ ይገኛሉ፡፡

ዛሬ ህወሃት/ኢህአዴግን ያስደነገጠው “አሸባሪ” በማለት የፈጠራ ክስ የመሠረተባቸው የከፈቱት የነፃነት ትግል ብቻ ሳይሆን ፊት የነሳው የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ እሙን ነው፡፡“አሸባሪ” ብሎ ተቀፅላ የሰጣቸው ድርጅቶችን ቁጥር ለመጨመር አሻንጉሊት ፓርላማውን ለመጥራት አላዳርስ ብሎት ይሁን ወይም “ስንቱን አሸባሪ ብዬ እዘልቀዋለሁ” ብሎ እፍረት ተሰምቶት፤ በፈጠራው ክስ የወነጀላቸውን ግለሰቦች በሙሉ “የግንቦት ሰባት አባል” ማለቱ ማብቂያ ለሌለው ውሸቱ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” በሚል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ ታላቅ ተስፋ ሰጪ በሆነ መመሪያ የሚተዳደረው የጋራ ንቅናቄያችንን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የግንቦት ሰባት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ” በማለት የዘባረቀው፡፡ ለመሆኑ የዚህ የ“አሸባሪነት” የፈጠራ ክስ የት ይሆን ማቆሚያው?

ከዚህ በፊት “የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉን” በተመለከተ በደወል ቁጥር 6 ላይ እንዲህ ብለን ነበር፡-

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከራሳችን ጀምሮ … (ማንኛውም ዜጋ) ህጋዊ የመብት ጥያቄ ካነሳ በዚህ ህግ መጠየቁ የማይቀር መሆኑን ነው። በተለይ እርስዎ የኢህአዴግ አባል እንደመሆንዎ በፓርቲዎም ሆነ ባጠቃላይ በመዋቅሩ ውስጥ የተሳሳተ አሠራር ተመልክተው የማስተካከያ ሃሳብም ሆነ ተቃውሞ ቢያሰሙ በዚሁ “የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ” ተከስሰው ቅጣት መቀበልዎ የማይቀር መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ምናልባትም የሚደርስብዎት ቅጣት እጅግ የከፋው እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ ይህ አደጋ በእርስዎም ላይ ያንዣበበ ነው፡፡

ከላይ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ የተጠቀሰውን የተናገረው በጸረ-ናዚነቱ የሚታወቀው ማርቲ ኒሞለር ነበር፡፡ “ብሔራዊ መነቃቃትን ሊያመጣ ይችላል” በማለት የናዚን ሥልጣን እርካብ ላይ መውጣት ሲደግፍ ቆይቶ በኋላ ግን የናዚ አሠራር መስመር መልቀቁን ሲያይ እጅግ በከረረ ሁኔታ የተቃውሞ ድምጹን ሲያሰማ ኖሯል፡፡ ታዲያ እርስዎስ “ለውጥ፣ ዕድገት፣ ሕዳሴ ይመጣል” በማለት እየሞተ ያለውን የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዓት ደጋፊና አባል ሆነው እስከመቼ ይቀጥላሉ? የህወሃት ጥቃት በጋዜጠኞች፣ በሠራተኛ ማኅበራት፣ በሰላማዊ ዜጎች፣ ወዘተ ላይ ሲሰነዘር ቆይቷል፡፡ እርስዎም እስካሁን “እኔን አይመለከተኝም” ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ ቀጣዩ በትር የሚሰነዘረው ግን በእርስዎ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ያኔ ምን ይሆን መልስዎ? ማንስ እንዲቆምልዎት ይጠብቃሉ?

ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ አገራቸውን ከምንም በላይ በሚወዱ ዜጎች ትመሠረታለች፡፡ ወንጀለኞችና ተባባሪዎቻቸውም በታሪክና በትውልድ ብቻ ሳይሆን በሕግም ተጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ ስለሆነም በተለይ በህቡዕ የሚካሄደው ትግል ወሳኝነት ያለው በመሆኑ ምልመላው ይቀጥላል፡፡ ሕዝባችን ከፈጣሪ የተሰጠውን ነጻነት እስኪጎናጸፍ ድረስም የእኛ ትግል አያቆምም፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF