Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 9

 

አራት ወይም አምስት የሚሆኑ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ጭው ባለ በረሃ ውስጥ በሚነደው አሸዋ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ። ከሞቱ ከብቶች የሰበሰቡትን አጥንት በተቀመጡበት ይቀጠቅጣሉ። በድሮው ቋንቋ ቅልጥም እየከሰከሱ ነው እንደሚባለው መሆኑ ነው። ውሃውን ከየት እንዳመጡት ባይታወቅም ባረጀ ቆርቆሮ ቀቀሉት፤ ተንተከተከ፤ ተፍለቀለቀ። ዙሪያው ተቀምጠው እያዩት ተንሰረሰረ። ፀሃይ ክው ያደረገው አጥንት ብስባሽ ስለሆነ አንዳችም ወዝ የሚባል ነገር አልነበረውም።

ይህንን አእምሮ የሚያፈነዳ፣ ህሊና የሚሰብር፣ እረፍት የሚነሳ፣ ነፍስን በሃዘን የሚያንጠለጥል፣ አጥንት ሰብሮ የሚገባ ዘጋቢ ምስል ያስተላለፈው አልጃዚራ ቴሌቪዥን ነው። ረሃብና ሃሩር ያነደዳቸው እነዚህ ያልታደሉ አዛውንቶች የሚኖሩት ኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ነው። ይህም ኑሮ ሆኖ በህይወት ለመሰንበት ከጋማ ከብቶች አስከሬን ላይ ከሰበሱት የደረቀ አጥንት ውስጥ መቅኔ ተገኝቶ መረቅ ሊጠጣ! አይ አፍሪካ፣ አይ መሪዎቻችን፣ እንዴት ይህንን ዘግናኝ ትዕይንት የተመለከተ ሰው ልቡ አይነካም? ከጥፋቱስ አይመለስም? ከዚህ በላይ ምን ልብ የሚያደማ ማስረጃ ለነፍሰ በላዎቹ ፖለቲከኞች ይቅረብ?

ለም በምትባለው አርሲ የጅቡቲ መንግስት ስንዴ እያጋዘ፣ የአካባቢው ተወላጆች አረም መብላት ደረጃ መድረሳቸው ይፋ ሆኗል። በቦረና መቶ ጋሻ የሚሆን መሬት ያለስራ ወፍ ዝር እንዳይልበት እየተጠበቀ ያካባቢው ከብቶች የሚግጡት አጥተው 75% የሚሆኑት የቦረና ከብቶች አለቁ። በኦጋዴን ረሃብ አንቆ የያዛቸው ህፃናት በጣር እየተሰቃዩ፣ ለነሱ እርዳታ የተላከ ምግብ አየር ባየር ሲሸጡ በጥቆማ የተያዙ አሉ። ጣር ሰንጎ ከያዛቸው ህፃናት ጉሮሮ ላይ ዝርፊያ! ምን አይነት ህሊና ያላቸው ናቸው እንዲህ የሚያደርጉት?

በከተማስ? በከተማማ ምንነቱና ፅዳቱ የማይታወቅ ትራፊ በጉርሻ እየገዙ የሚመገቡ ህፃናትና አዛውንቶች፤ ጉርሻ ተወዶባቸው የድንች ልጣጭ መብላት የጀመሩት እኛው አገር ነው። ለልጆቻቸው ምንም መግዛት ያቃታቸው አባቶች ልጆቻቸው ከተኙ በኋላ ሌሊት እየገቡ፣ ሌሊት እንደሚወጡ፣ በዚህም የተነሳ ልጆቻቸውን ማየት ያልቻሉ አባቶች እየበረከቱ መሆኑን የሰማነው መንግስት ከሌላት ሶማሊያ ሳይሆን ከአገራችን ኢትዮጵያ ነው።

አቡክተው መጋገር፣ ጋግሮ መቁረስ፣ አቁላልተው መወጥወጥ፣ አርሶ መጉረስ፣ የሰማይ ያህል የራቃቸው ወገኖች ሌማታቸው ደረቋል፤ ቦሃቃቸው አድርቷል። በደጉ ጊዜ የሰበሰቡዋቸው የማብሰያ ቁሳቁሶች እንደ ቅርስ እቃ ካገልግሎት ውጭ የሆኑባቸው ሚሊዮኖች ጠኔ ጠንቶባቸው ልጆቻቸውን ወደጎዳና በመላክ ስጋቸውን እንዲሸጡ መግፋት ያባትነትና የናትነት ወግ ሆኖባቸዋል።

ውሃ መርዝ የሆነባቸው ዜጎችም በአገራችን አሉ። ወንጂና መተሃራ፣ በጥቅሉ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሰፈሩ ወገኖች አልታደሉም። ፍሎራይድ የበዛበት ውሃ ስለሚጠጡ ጎብጠዋል። መተጣጠፊያቸው ደርቆ መዞርና መጠምዘዝ አይችሉም። በየቤቱ አስርና ከአስር አመት በላይ ያልጋ ቁራኛ ሆነው የኖሩ ሞት “ቶሎ የሚገል በሽታ” ናፋቂዎች ትንሽ አይደሉም። በ1997ዓም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አንድ የችግሩ ሰለባ “…ኤድስ ቢይዘኝ ይሻል ነበር። አስራ አንድ ዓመት አልጋ ላይ የጣለኝ ውሃ ነው። አጥንቴ ደርቋል። መገጣጠሚያዎቼ አይሰሩም። ያለ ሰው ድጋፍ የማደርገው ነገር የለም። የሚያሳዝነው እኔን በቁሜ የገደለውን ውሃ ልጆቻችን እየጠጡት አልጋ ተረካቢ መሆናቸው ነው። ተመልከተኝ ጥርሴ ተሸራርፎ አልቋል። የራሰ እንዳልበላ ብር የለኝም። ደረቁን እንዳልበላ ማኘክ አልችልም። አሁን እኔ ዜጋ ነኝ?...”በማለት ነበር እንባ እየተናነቃቸው የተናገሩት።

የዓይን እማኞች እንዳረጋገጡት ጎብጠው ፊደሉን “በ’’ የመሰሉ አሉ። ሲራመዱ አዋራ እየጠጡ ነው። ሰማዩን ከተመለከቱ ዓመታት ተቆጥሯል። አካባቢው ስለሚሞቅ በተኙበት ጠረናቸው ህይወት ያለው ሰው አይመስልም። ህይወታቸው ሲያልፍ እንኳን አስከሬናቸው በክብር አያርፍም። ሰውነታቸው ስለደረቀና ቅርፁን ስለቀየረ በሰላ መጥረቢያ ካልተቆራረጠ ሳጥን ውስጥ አይገባም። ብዙ ዘግናኝ ነገሮች አሉ።

ይህ ሁሉ የሚሆነው የምዕተ ዓመት የልማት ግብ አሳክተናል፣ ኢኮኖሚያችን ተመንድጓል፣ 2011 ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛው ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እናሰልፋለን ተብሎ በሚፎከርበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያን ህዳሴ ተግባራዊ እናደርጋለን በሚባል ባዶ ተስፋ እስከመቼ እንኖራለን? በጎሰኛ ፖለቲካ ታጅለን ከምንማቅቅ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚሆኑባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለማየት ወደ ጋራ ንቅናቄያችን በመቀላቀል ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በሚሰጠው ትግል ውስጥ የበኩልዎን የማድረጊያው ጊዜ አሁን ነው!!!

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF