Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 8

 

ያለንበት ወቅት በጠመንጃና በኃይል የሰው ልጆችን ረግጦ መያዝ እያከተመ ያለበት ነው። “እውነት አርነት ያወጣል” እንደተባለው በእውነት መምራትና ለእውነት መመራት እስከሌለ ድረስ የሰው ልጆች ማመጻቸውና “አንገዛም” ማለታቸው የማይቀር ሃቅ ነው። በዚህ የማይቀረው እውነት በርካታ አምባገነኖች ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ሲገደዱ አይተናል፤ እያየን ነው። ወደፊትም እናያለን፤ የዓለም አካል ነንና!

በፍቅር መተዳደር ሲባል ስርዓትን በመርህ አስደግፎ ማራመድ ማለት ነው። የመተዳደርና የማስተዳደር መሠረታዊ መርህ ደግሞ ሰላም፣ ነፃነት፣ በህዝብ ውሳኔ ማመንና እኩልነትን ማስፈን ናቸው። እነዚህ የአንድ ስርዓት መሰረታዊ ግብአቶች ሲረጋገጡ ህዝብ በመሪዎቹ ይኮራል። መሪዎች በህዝባቸው ይመካሉ። መልካም የሆነ የስልጣን ሽግግር ይኖራል።

እንዲህ ያለው ስርዓት ሲዋቀር ለግል ምቾትና ብልፅግና የመኖር “ትራፊ” አስተሳሰብ ስለማይኖር መሪና ተመሪ እንዲሁም መሪዎች እርስ በርሳቸው አንዱ ከሌላው ራሱን ለመጠበቅ የደህንነትና የአፈና ተቋም በማቋቋም የአገር ሃብት አይማግዱም። ይልቁኑም አደራ ለሰጣቸው ህዝብ ጥቅም ያውሉታል እንጂ። በየመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች በነፃነት እየሰሩ ለእውነት በመኖር በየትኛውም ስርዓት አርነት የሚያወጣቸውን መልካም ተግባር ለተተኪው ትውልድ ያስተላልፋሉ።

በአግባቡ የተዋቀረ ስርዓት ያላቸው አገሮች ከህዝብ የሚሰጣቸውን የተገደበ ስልጣንና የተገደበ የስልጣን ጊዜ ባግባቡ ለመጠቀም የቻሉት በዜጎቻቸው ፍፁም ቀናነት፣ አገር ወዳድነትና ህዝብ አክባሪነት እንጂ በተለይ ልዩ ከሆነ መለኮት ተቀብለውት አይደለም። እኛ ለምን ለዚህ አልታደልንም?

ከክርስቶስ ልደት በፊት ይታረስበት በነበረ ማረሻ የሚጠቀም አርሶ አደር ልጆች ነን። ዛሬ ድረስ በቀን ሶስቴ ቀርቶ አንዴ መብላት ያቃተን ህዝቦች ነን። ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ተስኖን በውሃ ወለድ በሽታ በቀን በሺዎች የሚረግፉባት አገር ባለቤት ነን። ስራ መፍጠር አቅቶን በድህነት የምንሰቃይ ነን። መሰረታዊ ፍላጎቶች ቅንጦት የሆነብን ህዝቦች ሆነን በልመና የአንድ ትውልድ ዘመን በላን። በገጠር፣ በከተማ ችግር የጠበሳቸው ህዝቦች ተብለን በችጋር፣ በድርቅና በረሃብ ትርጉም መከራከሪያ ሆነናል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎን እስር፣ ግርፋት፣ አፈና፣ ስደት፣ ባይተዋርነት፣… ነግሶብናል። እስከመቼ በዚህ ይቀጥል?

ፖለቲከኛ መሆን ማለት ራስን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ ማለት ነው። ራስን በማቅለጥ ለሌሎች ብርሃን ለማድረግና ለተተኪ ትውልድ ያቺን “ዋጋ” ተከፍሎባት እዚህ የደረሰችውን ኢትዮጵያን በተሻለ ደረጃ ለማስረከብ መማል ማለት ነው። ታዲያ ማን ይህን እንዲያደርግ ይጠበቃል? ለህዝባችንም ለኛም ማን ይምጣልን? ለአገራችን ተቆርቋሪ ከየት ይፈለግ? እድሜ ልካቸውን በችግር ድሪቶ ውስጥ ለሚማቅቁት ያገራችን ምስኪኖችና ምንዱባኖች ማን ይድረስላቸው?

ተቃዋሚ ባይኖርም እንኳ እያንዳንዱ ሥርዓት እንዳፈጣጠሩ መበስበሱና መሞቱ አይቀርም። አገርም፣ ተተኪ ትውልድም፣ የእርስዎም ልጆች ይቀጥላሉ። አቶ መለስም፣ ህወሃትም፣ ኢህአዴግም፣ ድቃይ ድርጅቶቹም፣ ሥልጣኑም፣ ሃብቱም፣ ክብሩም፣ ሁሉም ያልፋሉ። አሁን ሥርዓቱ እየፈፀመ ካለው ግፍ አንፃር የህወሃት/ኢህአዴግ እድሜ መሪው እንደነገሩን 50 ዓመት ይሞላል የሚል ግምት ይኖርዎታል ብለን አናስብም። ስለዚህ ዛሬም ጥሪ አለን።

የለውጥ ሃይሎች እርስዎን ከሚመስሉ አገር ወዳዶች ጋር በመሆን በአገራቸው የማይቀረውን ለውጥ ለማምጣት ሌትተቀን እየደከሙ ነው። ባለን መረጃ መሰረት በጣም ከሚቀርቧቸው ጋሻ ጃግሬዎቻቸውና የአፈና ኃይሎቻቸው በስተቀር አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት በአቶ መለስ  አገዛዝ እየተሸማቀቁ ነው። የፍርድ ቀን በራሳቸው አውጀው የተቀመጡም አሉ። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ እንዲህ ያለው የአሳሪና የታሳሪ ፖለቲካ ተቀይሮ በአገራችን ላይ ዕርቅ ሰፍኖ የማየት ታላቅ ራዕይ አለው። ለዚያም እየሠራ ይገኛል፡፡

ከጎሳ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጠው የጋራ ንቅናቄያችን እርስዎም የዚህ ራዕይ ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀርብልዎታል። ኢትዮጵያ ነጻ ትወጣለች፤ ነጻ የምትወጣው ግን በሌላ ነጻ አውጪ ሳይሆን ነጻ አውጪውንም ጭምር ነጻ በሚያወጣው እውነት ነው፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF