Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 7

 

በርግጠኛነት ኔልሰን ማንዴላን አይጠሏቸውም። የኔልሰን ማንዴላን ታሪክ ሲያነቡ “የማንዴላን ዓይነት ክብርና ዝና ያለኝ ሰው ብሆንስ?” ብለው ሊመኙ ይችላሉ። የእኛም እምነት እርስዎ “ሌላው ኢትዮጵያዊ ማንዴላ መሆን፤ እውነተኛ ንብ መሆን ይችላሉ” የሚል ነው።

ሜታሞርፎሲስ (ልውጠተ ቅርጽ) የበራሪ ነፍሳት ዜና ህይወትን የሚያሳይ የሳይንስ ቅንጣቢ ክፍል ነው። ነፍሳቶቹ በዚህ ዑደት ውስጥ አልፈው ከእንቁላልነት ወደ እጭ፣ ከእጭ ወደ ትል፣ ከትል ወደ ሙሉ አካልነት በመቀየር ትክክለኛ መጠሪያቸውን ይይዛሉ:- ዝምብ፣ ንብ፣ ተርብ፣ ጢንዚዛ፣ አንበጣ፣ ወዘተ፡፡ አፈጣጠራቸው ሜታሞርፎሲስ በመሆኑ ይመሳሰላሉ። በግብር ግን ሁሉም ይለያያሉ። በዚህ ልውጠተቅርስ ከሚፈጠሩት ነፍሳቶች መካከል ንብ ትልቅ ስፍራ ያላት፣ የመልካምነት መገለጫ የሆነች፣ በስሟ የተቀደሰላት፣ ብዙ የተባለላት ፍጡር ናት። መንጋዎቹ ስርዓት ጠብቀው የሚኖሩ፣ በህብረት የሚሰሩ፣ ከቆሻሻ ውስጥ መልካም ነገር መርጠው በማንሳት የሚታወቁ፣ ለሥራቸውና ለመሪያቸው ታማኝ የሆኑ፣ መሪያቸውም የሚተማመንባቸው፣ ሰላይና ሰራዊት የማያሰማራባቸው የኅብረት ተምሳሌቶች ናቸው።

ንብ ቀፎዋን አታስነካም። ቀፎ በአገር፣ በአገር ሃብት ይመሰላል። ንቦች በኅብረት የሚያመርቱት ማር ለአገርና ለሕዝብ በሚቀርብ የኑሮ ግብአት ይመሰላል። በንቦች የሥራ ክፍፍል አንዱ በሌላው ስራ ጣልቃ አይገባም። ንብ በውሃና በጭስ ካልተሸበረች በስተቀር ማርዋን አታስነካም። ንብ ካልተመቸው ነቅሎ ይሄዳል። ሌላ ቤት ይሰራል። አገሩን ጥሎ፣ ድንበር ተሻግሮ ግን አይሄድም። ንብ አውራውን ተከትሎ ሲነሳ፣ አዲስ ቦታ ሄዶ ሲከትም፣ ብቻውን የሚቀር የንብ ዓይነት አለ። እንዲህ ያለው ንብ እንደ ዋናዎቹ ንቦች መረጃ የለውም። ስራው ውሃ መቅዳትና ውሃ ማመላለስ ብቻ ነው። ይህ ንብ “ድንጉል” የሚባለው ነው። እንዲህ ተብሎለታል፡-

“ንብ ሄደ፤ አውራው ሄደ፤ ያውም የወለደው፤

ከቤቱ የቀረው ድንጉል ድንጉሉ ነው፤ ቂጡ የከበደው፤”

ልብ ይበሉ  ህዝብ ያልተቀበለውና “በቃህ” ያለው መንግስት፣ ህዝብን በኑሮ፣ በእስር፣ በግርፋት፣ አስገድዶ በመድፈር፣ ንብረቱን በመቀማት፣ እኩል ባለማስተዳደር፣ መሬቱንና ድንበሩን በመቁረስ፣ የሚያሰቃይ አገዛዝ የህዝብ ቁጣ ይነድበታል። የህዝብ ቁጣ የነደደበት መንግስት መጨረሻውም ውድቀት በመሆኑ ሽሽት ሲጀምር ጭፍራውን አራግፎ ነው። ጭፍራውም ብቻውን ሲቀር ህዝብ እጅ ይወድቃል።

የቀድሞው የህወሃት መስራች አቶ ገ/መድህን አርአያ “ታላቋ ትግራይ እየተሰራች ነው። ሩጫውም ታላቋ ትግራይ መተንፈስ ስትጀምር ሌሎች መተንፈስ እንዲያቆሙ ማድረጉ ላይ ነው” ብለዋል። ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነ አስተውለዋል? አቶ ገ/መድህን ይህን ያሉት የትግራይ ህዝብ እንዲህ ካለው ታሪካዊ ውርደት ራሱን እንዲያገል ነው። እርስዎስ በዘረኝነት ሣጥን ውስጥ ገብተው ጠብበዋል ወይስ ሰብዓዊነትን ከዘረኝነት በፊት ያስቀድማሉ?

ስለዚህ እውነተኛ ንብ መሆን የወቅቱ አጀንዳ ነው እንላለን። የውሃ ቀጂነቱን ሥራ በመቀየር እንደ ንብ አውራ የመሪነት “ጀዝም” መያዝ ግድ ይላል። የፈለገው ዓይነት ረሃብ ቢመጣ ነፍስ የዘራበትን እጭ የማይበላውን ንብ በመሆን ሕዝባዊ ወገንተኛነትን በችግር ወቅት ማሳየት ይጠበቅብዎታል። በችግር ወቅት ነገ አብሮዎት ለሚቀረው ወገን ማር በመሆን ከከሃዲዎች ጎራ በመለየት እውነተኛ ንብ ይሁኑ፡፡

ንብ በመስዋዕትነትም ትታወቃለች። ጠላትን ለመከላከል፣ አገሯን (ቀፎዋን) ከጠላት ለመጠበቅ አታወላውልም። “የወደፊቱ አይታይም” በሚል ፍልስፍና ንብ ህልውናዋን፣ ቤቷን፣ ማሯን፣ እጯን፣ እንጀራዋን… አሳልፋ አትሰጥም። እውነተኛ ንብ መሆን የወቅቱ ጥሪ ነው የምንለውም ለዚህ ነው። የጋራ ንቅናቄያችን ለሰብአዊነት ቅድሚያ በመስጠት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚያደርገው ትግል ውስጥ ቦታ አለዎት። የእርስዎ ትክክለኛ ንብ መሆን ለልጅ ልጅ ታላቅ ተስፋ ነው፤ በቀለ ወያ እንዳሉት “የከበረ ስማችሁ በልጆቻችሁና በወገኖቻቸሁ ዘንድ ሲመሰገን በታሪክም ሲጠራ ይኖራል።”

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF