Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 6

 

አሁን በሀገራችን ባለው ሁኔታ በሽብርተኝነት ስም እየወሰደ ያለው እርምጃ ሽብርተኝነትን ከሕዝብ ጋር ሆኖ ከመከላከል ይልቅ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው የሽብር፣ የፍርሀትና የመሸማቀቅ ድባብ፣ የበለጠ አመዝኖ ይገኛል፡፡ ሁኔታውም የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያጠብ፣ ከሕዝብ ጋር መቃቃርን የሚፈጥርና ሽብርተኝነትን ከመቆጣጠር ይልቅ የሕዝብንና የፖለቲከኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያለመ ነው፡፡

ፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ በአምባገነን ሥርዓቶች በሚመሩ አገሮች ውስጥ አደገኛ  ነው፡፡ በዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚመሩ አገሮች ፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የሚያተኩረው የውጭ አደጋን በመከላከል ላይ ነው፡፡ ከሥርዓቱ አሳታፊነትና ፍትሐዊነት የተነሳ በዘላቂነት የሚፈራ አደገኛ የውስጥ ጠላት የሚሉት ኃይል አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ ሕጉ ሲወጣ የዜጎቻቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለአግባብ እንዳይነኩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡

በአምባገነን ሥርዓት በሚመሩ አገሮች ግን፤

  • አምባገነኖቹ ኃይሎች የውጭ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ጠላትም እንዳላቸው ስለሚያምኑ
  • በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ነፃ ጋዜጦችን እንደጠላት ስለሚያዩ
  • ማንኛውም ቆንጠጥ የሚያደርግ ትችት እንደ ጠላትነት መግለጫ ተደርጎ ስለሚወሰድ

አዋጁን የሚያወጡት የውጭ ጠላትን ብቻ ሳይሆን የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውንም ለማጥቃት በሚያመቻቸው መልክ ነው፡፡ በመሆኑም አምባገነን መሪዎች የሚቀርፁት ሕግ፤

  • ለደህነትና ለፖሊስ ከሞላ ጎደል ያልተገደበ የመያዝ፣ የመፈተሸ፤ የማሰር ሥልጣን እንዲሰጥ
  • አንቀጾች ለገዢዎች በሚያመች መልክ ለመተርጎም እንዲያመቹ አሻሚ ባህርይ በመሰንቀር
  • አንድ ድርጊት የሚያስቀጣ ወይም የማያስቀጣ መሆኑ በእርግጠኝነት እንዳይታወቅ በማድረግ

ያወጣሉ፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች፣ ጋዜጦች ሕዝቡ በአጠቃላይ ዘወትር በስጋት ላይ ይሆናሉ፡፡ የፍርድ ሥርዓቱ በቁጥጥራቸው ሥር ስለሆነ የተፈለገውን የርምጃ ትዕዛዝ ለመስጠት ወይም ሥርዓቱ በሚፈልገው መንገድ ለመፍረድ ታዛዥ ይሆናል፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከራሳችን ጀምሮ ከቤተሰባችን፣ ከዘመዶቻችን ወይም በቅርብ ከምናውቃቸው ሰዎች አንዱ ህጋዊ የመብት ጥያቄ ካነሳ በዚህ ህግ መጠየቁ የማይቀር መሆኑን ነው። በተለይ እርስዎ የኢህአዴግ አባል እንደመሆንዎ በፓርቲዎም ሆነ ባጠቃላይ በመዋቅሩ ውስጥ የተሳሳተ አሠራር ተመልክተው የማስተካከያ ሃሳብም ሆነ ተቃውሞ ቢያሰሙ በዚሁ የ‹‹ፀረ ሽብርተኝነት›› ሕግ ተከስሰው ቅጣት መቀበልዎ የማይቀር መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ምናልባትም የሚደርስብዎት ቅጣት እጅግ የከፋው እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡

ስለዚህ ይህ አደጋ በእርስዎም ላይ ያንዣበበ ነው፡፡ ሕዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው ‹‹የፀረ-ሽብርተኝነት›› አዋጅ ከበርካታ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ  ሳይሰጠው እንዲለወጥ፤ በ‹‹ፀረ-ሽብርተኝነት›› ሕግ ስም የሚደረገው የሕዝብ መብት ረገጣና እስራት በአስቸኳይ እንዲቆም መታገል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። የራሱን ሕገመንግሥትና መመሪያ እየጠቀሱ መታገል መቻሉንም እኛ ልናሳስብዎት አይገባንም፡፡ ይህንን እያወቁ ሳያደርጉ መቅረት ግን የኅሊና ወቀሳ የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን ጊዜውን ጠብቆ በሕግ ማስጠየቁም አይቀርም፡፡

ትላንት ዛሬ አይሆንም - አልፏልና፡፡ ዛሬም ነገ አይሆንም - ገና አልመጣምና፡፡ የሰው ልጅ ማንነት የሚለካው ትላንት በፈጸመው ወይም ገና ወደፊት ሊፈጽም በሚያስበው አይደለም፡፡ አሁን፣ ዛሬ በእጁ ላይ ባለው ነው፡፡ ዛሬ በሚወስነው ውሳኔ እና በሚፈጽመው ተግባር የነገ ማንነቱን ያጸናበታል፡፡ ከሕዝብ ጋር የመቆሚያው ጊዜ ዛሬ - አሁን ነው፡፡ ዛሬን በማንአለብኝነት አሳልፎ ነገ ‹‹አድኑኝ›› ብሎ መማጸን የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም ነው፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF