Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 5

 

ኢትዮጵያ ምኞታቸው፣ ተስፋቸው፣ ስብዕናቸውና ሥነልቦናቸው በተሳሰረና በተዛመደ ከጥንት ጀምሮ ተከባብረ ው በሚኖሩ ሕዝቦች የተመሰረተች ሉዐላዊ አገር ነች። ሕዝቦቿ  በደስታም ሆነ በሐዘን፣በተድላም ሆነ በችግር፣በሞገስም ሆነ ሲገፉ፣ ባገርም ሆኑ በስደት የኢትዮጵያዊነታቸውን ማተብ አጥብቀው የሚይዙ ናቸው። መንግስታት ሕዝቦችን የመነጣጠልና አንዱን የበላይ አንዱን የበታች በማድረግ ስልት ይጠቀሙ በነበረው ወራዳ የአገዛዝ ዘዴ ምክንያት የታዩ መቃቃሮች ሕዝቦች ለአገራቸው ያላቸውን የእኔነት ስሜት ያቀዛቀዘበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም በመሰረታዊ አስተሳሰብ ሉዓላዊ ማንነቱን በማክበር ይታወቃል።

ከገዥዎቹ ፍላጎት ውጪ ተናንቆ እንዳይገናኝ ሲያደርጉ ተፈላልጎ እየተጋባና እየተዋለደ ፣ ተጠላልቶ እንዲራራቅ ሲፈልጉ ተጠራርቶ ተደባልቆና ተሳስቦ በማህበራዊ መስተጋብር ተቋሞቹ ተባብሮና አብሮ ሰርቶ የኖር ሲሆን በኢትዮጵያዊነት ክብርና ኩራት የሚያምነው የዛሬው ትውልድም ይህን ክብርና ኩራት ጠብቆ ከቶውንም ከአበው ፋና መዛነፍ ሳያሳይ፣ ከዓላማው መዘናጋትና መሳሳት ሳይኖር ሊቀጥል ቃል ገብቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነት የኖረ፣ ነፃነት አፍቃሪ፣ ለነፃነቱ ፍጹም ታጋይ፣  አትንኩኝ ባይ፣ መብቱን አፍቃሪ፣ አገሩን ከውጭ ወራሪ ኃይልችና ከውስጥ አዋኪዎች ተከላክሎ፣ ጠብቆና አስከብሮ በብሔራዊ አንድነቱ ታፍሮና ተከብሮ የኖረ ሕዝብ መሆኑን በአለም ኅብረተሰብ ፊት  ታሪኩ የተመሰከረለት ነው፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ ቀንዓዊ ከመሆኑም ባሻግር እነዚህ የዕልውናው ምክንያት የሆኑ ዕሴቶች ተጠብቀውና ተከብርው እንዲኖሩ ደረጃ በደረጃ መወሰድ የሚገባውን እርምጃ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን የዘነጋ ይመስላል። የህዝቡን መብት ለማስከበር በቡድንም ሆነ በተናጥል ጥያቄ የሚያነሳ ኃይል ብቅ ሲል ህወሃት/ኢህአዴግ የማጥፊያ ሰይፉን መዞ "ህግ መንግስቱን ሊንዱ"፤ "የህዝቡን ሰላም ሊያደፈርሱ"፤ "ሽብር ሊነዙ"...ወዘተ እያለ ሲያስፈራራ፣ ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሲያሳድድ ይታያል። ህወሃት/ኢህአዴግ ማስፈራሪያ የሚያደርገው ህገ መንግስት የህዝብ መብት ማስከበሪያ፣ ነፃነት ማስጠበቂያ መሣሪያ ሆኖ ካላገለገለ የመፍረሱ ወይም የመሻሻሉ ዕጣ የማይቀርለት የመለኮት ቃል አለመሆኑን  ለምን ይዘነጋል።

ሕዝቦች መብታቸውን ለማስከበር ያደረጓቸው ትግሎች "ካልደፈረሰ አይጠራም" እንዲሉ ሰላም  ደፍርሶ ከባሰ ደግሞ ደም ፈሶ መሆኑን ዘንግቶ ነው ዛሬ ህወሃት/ኢህአዴግ ስለ ሰላም  መከበር አቀንቃኝ በመሆን የነፃነት ትግል ሂደትን የሰላም ማደፍረስ ተግባር አድርጎ የሚያላዝነው።

ያ የሚፈራው የህዝቦች ንቅናቄ አፍጥጦ ሲመጣበት ወደ አደገኛ አሸባሪ ቡድንነት የተቀየረው ራሱ ኢህአዴግ ነው። እውነትን በመፃፋቸው መአት እንዳመጡ አድርጎ ያሰራቸው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና አምደኛ ርዕዮት ዓለሙ የህወሃት/ ኢህአዴግ የድንጋጤ ዕብደት ሰለባዎች ናቸው። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ እዉቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት አቶ አሳምነው ብርሃኑ እና አቶ ናትናዔል መኮንን፣ የመላው ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል ዘመኑ ሞላ፣ አንጋፋው የኪነት ባለሞያው የሆኑት አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረሱ ኦልባና ሌሊሣ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑትና የኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀ መንበር በቀለ ገርባ የሚመሩት ትግል ህዝባዊ መሆኑን እና ከኋላቸው ያሰለፉትን ኃይል ሊቋቋመው እንደማይችል ያወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎቹንና ቀላጤዎቹን አስሮ በሀሰተኛ ክስ “አሸባሪ ናችሁ” ማለቱ በጭንቀት የመንፈራገጡ ማሳያ ነው።

“በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በተቃውሞው ጎራ የሚገኙ የተገነዘቡት አንድ ጉዳይ ዝም ብሎ በሆይ ሆይታ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ብሎም ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ነው፡፡ በቆራጥነት፣ በፅናትና አርቆ በማየት ነው ለድል መብቃት የሚቻለው፡፡ ሰላማዊ ትግል ሲባል ሞት፣ እስራትና እንግልት የለም ማለት አይደለም፡፡ ልዩነቱ ሰላማዊ ታጋዩ አይገድልም፡፡ ሠላምን አያደፈርስም፡፡ ነገር ግን በፀናና በተደራጀ ሁኔታ መብቱን ይጠይቃል፡፡ ሉዓላዊ ስልጣኑን ዕውን ሳያደርግ ወደ ኋላ አይመለስም፡፡ በሠላማዊ ትግል ውጤታማ እንዲሆን የሕዝብ አንድነትና የዓላማ አንድነት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ትግሉ የራሱ ስነምግባር አለው፣ መደጋገፍን ይጠይቃል፡፡ አንዱ ሲወድቅ እሱን አንስቶ ከፍ ባለ የሞራልና የዓላማ ልዕልና ትግሉን እየተቀባበሉ ወደፊት መሄድ ይጠይቃል፡፡ አስቀድሞ የነፃነትን ምንነትና የሚከፈለውን ዋጋ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አሁን የጀመርነው ትግል ግብታዊ ያልሆነ የተጠናና በስሜት የማይነዳ ሰላማዊ ትግል የአንድ ቅፅበት ግርግር  እንዳልሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ ሊረዳ ይገባል።”

ከእንግዲህ የሚሰማህን ሰቆቃ በቃ ልትል ይገባል፡፡ የአገር ባለቤትነትህንና የዜግነት መብትህን፣ ክብርህን ለማስጠበቅ ከሁሉም ጋር ሆ ብለህ መነሳት አለብህ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሕግ የበላይነት ተከብሮ “ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነት የቀደመበት” ህዝባዊ መንግሥት የሚቋቋምበትንና አዲሲቷ ኢትዮጵያ” የምትመሠረትበት አጋጣሚ አሁን ነው፡፡

እርስዎ ወደውም ይሁን ተገደው የህወሃት/ኢህአዴግ መሣሪያ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ሆይ! የማንነትዎ መገለጫው፣ ክብርና ሞገስን የሚያጎናፅፍዎ ዛሬ እያገለገሉ ያሉትን ህወህት/ኢህአዴግን በመክዳት ለህዝባዊው ትግል አለኝታነትዎን መግለፅ ነው።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF