Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 4

 

በአዲስ ዓመት ብዙ ሰዎች በርካታ ዕቅዶችን ያወጣሉ፤ ብዙ ህልሞችን ያልማሉ፤ አያሌ ምኞቶችንም ይመኛሉ፡፡ ጭንቅላቱ ላይ አንዲት የጸጉር ዝርያ የሌለው ራሰ-በራ ‹‹በዚህ አዲስ ዓመት በየወሩ ደመወዝ ስቀበል ጸጉሬን በመስተካከል ውበቴን እጠብቃለሁ›› በማለት ለሚያወጣው ዕቅድ ‹‹እንዳፍህ ያድርግልህ›› ብለው ባልጀሮቹ ‹‹ቢመርቁት›› በጥርሱ ብቻ ሳይሆን በመላጣውም ጭምር እየፈገገ ‹‹አሜን›› በማለት ምላሽ ቢሰጥ የራሰበራነቱን እውነታ አይቀይረውም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የዛሬ 20ዓመት የገቡትን ቃል መወጣት ያቃታቸው የህወሃት መሪዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ እየተራበ በዚህ አዲስ ዓመትም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዳሴ ጉዞ ይቀጥላል፤ ሕዝቡም ጠግቦ ያድራል›› በማለት ‹‹ባዶ ተስፋ›› ቢሰጡም ዓይኑን ያፈጠጠውን ሐቅ የትም ሊሸሽጉት አይችሉም፡፡

ዛሬ የህወሃት/ኢህአዴግ አባል በመሆንዎ ብቻ ባገኙት ሥልጣን ወይም ከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ በመሆን ሀገሪቱ ከመጠን ባለፈ ድህነት ውስጥ በመግባቷ  ህዝቦቿ በኑሮ ውድነት ምክንያት ተራቡ፣ ታረዙ፤ ገበሬው ህግ በማይገዛቸው የህወሃት/ኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች በግድ በውድ ዋጋ ብድር እንዲወስድና ካመረተው ምርት በግድ እንዲከፍል ተደርጎ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሲሶ ተከፋይ ዘመናዊ ጢሰኛ ሆኗል ተብሎ የኢህአዴግ ፖሊሲዎችን ክስረት ሲነገር ሲሰሙ ላያስደስትዎ ይችላል። እውነታውን ግን እርስዎ የሚያውቁትና  ጥቅምዎ እንዳይቀርብዎ ሲሉ እያዩ እንዳላዩ ከመሆንዎ ባሻግር የህሊናዎ ክስ ቢበዛብዎትም በፍርሃት ተከበው ‹‹የአይጥ ምስክር ድንቢጥ›› እንዲሉ ተቃዋሚዎችን ‹‹አፍራሾች፣ ሁከት ናፋቂዎች፣ ሥልጣን ፈላጊዎች›› በማለት አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ሊያጣጥሉ ሲሞክሩ ይታያሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው ሞልቶለት ሳይሆን ባለበት የሰብዓዊ መብት አፈና ምክንያት እየደረሰበት ያለውን ግፍና በደል መናገር ያልቻለበት ሁኔታ መኖሩን፤ ብሶቱን  የሚናገር ሲኖር ደግሞ እንደ ፀረ ሕዝብ ተቆጥሮ ወደ ወኅኒ ቤት እንደሚወረወር ያውቃሉ።

ይህ እርስዎ አባል ሆነው የሚያገለግሉት የህወሃት/ኢህአዴግ በድህነት የተቀፈደደው ሕዝብ ምን እንዳለ፣ ምን እንደተነፈሰ እንዲሰልሉ እያደረገዎ መሆኑን ያውቃሉ። ወሬ ቃርሞ ማቅረብ የአባልነት ግዴታዎ በመሆኑ የሚሰሙትን የህዝብ ዕሮሮ ድምፅ የአመፅ መነሳሳት አድርገው ወንጅለው በማቅረብ ስንቶችን ለእስር፣ ለግርፋትና እንግልት፣ ለስደትና ሞት እየዳረጉ የህወሃት/ኢህአዴግ ታማኝ ሆነው እየኖሩ ነው። በቅርቡ በተለቀቀው የዊኪሊክስ ዘገባም መሠረት በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በእስር እየማቀቁ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን በዘመነ ደርግ ይደረግ የነበረው ዓይነት ማሰቃየትና ግርፋት እንደሚደርስባቸው አጋልጧል፡፡ እንደ ቀይመስቀል ያሉትን ዓለምአቀፍ ድርጅቶችን የእስርቤት ጉብኝት እንዳያደርጉ በማገድ እስረኞችን እጃቸውን ሽቅብ ከጣራ ጋር በሠንሰለት በማሰር፣ ውስጥ እግራቸውን በመግረፍ፣ ወንዶቹን ብልታቸው ላይ ክብደት ያለው ዕቃ በማንጠልጠልና በማሰቃየት ታሳሪዎቹን አናዝዞ መረጃ ለማግኘት መሞከር የኢትዮጵያ እስርቤቶች አይነተኛ መገለጫ መሆኑ ዘገባው ማስረጃ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ይህ እንግዲህ እነ አቶ መለስ ደርግ ‹‹ሰው በላ ስርዓት›› ስለሆነ ‹‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም›› ሲባል ያቋቋሙት ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት›› እያደረገ ካለው ኢሰብኣዊ ተግባር ጥቂቱ ነው፡፡ እርስዎ ግን ይህንን ሁሉ እውነታ እያወቁ የዚህ አገዛዝ ደጋፊና አባል ሆነው ሲቀጥሉ ምን ይሰማዎታል? እስከመቼስ ህሊናዎን ጨፍልቀውና እውነትን ረግጠው ይኖራሉ?

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ትናንት ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ይታገሉ የነበሩና ሥልጣን እንደያዙ ይህን ዓላማ ለማሳካት አፍታም ሳይቆዩ 1983 ከወሎ ተነጥቆ ትግራይ የተጨመረውን የአሸንጌ ባህርን፣ የወራ ውሃንና ኮረምና አማላጣን የሚያካትተው ለም መሬት፣ በ1983 እአአ  ከጎንደር ተነጥቀው የተወሰዱትን የሁመራ፣ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የዋልዴባ ክልል፣ ብራ ዋስያንና ጠለምት መሬቶች፤ በ1994 በአማራው ክልል ከነበረው ከጠገዴ ክፍሌ ግጨው የተባለው የእርሻ ቦታና አብደራፊ ከተማን የሚያካትተው የታች አርማጭሆ የእርሻ መሬት ነው። ምንም እንኳን ህወሃት/ኢህአዴግ ‹‹ኅብረብሔራዊ ነኝ›› እያለ ቢደሰኩርም ይህ ድርጊቱ ብቻ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዐይን የማያይና ለአንድ ብሔር የበላይነት የሚሰራ ለመሆኑ አስረጂ ነው። ይህንን እኩይ ተግባሩን ለመፈጸም ደግሞ ንጹሐን የትግራይ ተወላጆችን እየተጠቀመ መሆኑ ዓይን ያወጣ ሃቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ንቅናቄያችን ዘር ሳይለይ ባጠቃላይ ለሰብዓዊነት የሚታገለው፡፡    

ህወሃት/ኢህአዴግ በጋምቤላ ሕዝብ መካከል ልዩነትን በመፍጠር የጠላትነት ስሜት በውስጣቸው እየዘራ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚጠነስሰው ሴራ ሲነቃበት ጠንክሮ የተቃወመውን ብሔር ለይቶ ዘር ያጠፋ አገዛዝ ነው። የጋምቤላ ሕዝብ  የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱን ለማስከበር ትግሉን አጠናክሮ ሲቀጥል ሕዝብን አጠቃሎ እንደጠላት በመፈረጅ ከመሬቱ እንዲፈናቀል በማድረግ በድህነት እንዲቆራመድ፣ አገሩን ትቶ እንዲሰደድ ለማድረግ መሬቱን ለውጭ አገር ባለሃብቶች በወደቀ ዋጋ እየቸበቸበ ይገኛል።

ኢህአዴግ የኦሮሞን ሕዝብ ጠቅሎ እንደ ሽፍታ የሚፈርጅ አገዛዝ ነው። ጥቂት ለሆዳቸው ያደሩ የብሔሩ ተወላጆችን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት የሚታገሉ የኦሮሞ ድርጅቶችን እንደ አሸባሪ፣ የብሔሩ ተወላጆችን እንደ ነፍሰ ገዳይ ያሳድዳቸዋል። ዛሬ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የኦሮሞ ልጆች በህወሃት/ኢህአዴግ እስር ቤቶች እየማቀቁ ይገኛሉ። ይህን እውነታ እያወቀ፣ እያየና እየሰማ የህወሃት/ኢህአዴግ አባል በመሆን እየተፈፀመ ላለው ወንጀል ተባባሪና አድራጊ የሆኑ የኦሮሞ ልጅ መኖር የለበትም። ራስዎን የሚጠይቁበት ወቅት አሁን ነው። በእንደዚህ ዓይነት ኅሊና እስከመቼ ድረስ ነው የሚኖሩት?

ህወሃት/ኢህአዴግ የኦጋዴን ሕዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ጭቆና ስላንገፈገፈው የሚያደርገውን ትግል ለማኮላሸት በቦንብ መኖሪያውን አቃጥሏል፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሞበታል። በዚህ አልበቃውም ተብሎ በህወሃት/ኢህአዴግ ደካማ ፖሊሲ ምክንያት በተከሰተ ድህነት መቆራመዱ ሳያንሰው በተፈጥሮ ድርቅ ተመትቶ ረሀብና ወረርሽኝ ሲያጠቃው ከለጋሾች የተገኘ ዕርዳታ እንኳ እንዳያገኝ በማድረግ አንድ የህዝብ ክፍል ዕልቂት እንዲደርስበት በማድረግ ላይ ይገኛል። እርስዎም የህወሃት/ኢህአዴግ አባል በመሆንዎ የዚህ በትውልድ ምህረት በማያገኝ ወንጀል ተባባሪና ተሳታፊ እንደሆኑ መዘንጋት የለብዎትም።

የህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች የአማራን ሕዝብ እንደጠላት የሚፈርጁና ለመብቱ በመታገል አልበገርም ባይነቱን ሲያሳያቸው ‹‹አንድ ዓይኑን አጥፍተን ሁለተኛውን ባለማጥፋታችን አንሰራራብን›› ብለው በፀፀት በአደባባይ የሚናገሩና ቢችሉ ይህን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከምድረ ገፅ ከማጥፋት ወደኋላ የማይሉ ናቸው። ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሣሣት በማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም ከሚፈልግ ኢህአዴግ እንዲሁም ህዝብን በጥቅል በጠላትነት በመፈረጅ አንድ ቀን መውጪያ ቀዳዳ ሲያጣ  ኢንተርሐምዌ የጥፋት በትሩን ሊሰነዝር ከተዘጋጅ ህወሃት/ኢህአዴግ ጋር በአባልነት መቀጠል አዕምሮ የሌለው ሰው ውሳኔ ነው።

ስለዚህ ለሰብዓዊ ህሊናም ሆነ ለመንፈሣዊ ስብዕናዎ ከሚቀፍ ተግባር ለመራቅ የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ ለመገርሰስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሣታፊ በመሆን ከተጠያቂነት ለመዳን ተነሳሽነት እንዲኖርዎ ያስፈልጋል። የጋራ ንቅናቄያችን ‹‹ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነት የሚቀድምባትን›› እና የእያንዳንዱ ሰው የግል መብት የሚከበርባትን ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ›› በመመሥረት በጭቆና ሥር የሚገኘውን የአገራችንን ሕዝብ ነጻ የማውጣት ተግባር በዚህ አዲስ ዓመት በንቃትና ትጋት ያከናውናል፡፡ ይህ ዕቅድም እንደ እርስዎ ያሉትን ‹‹መውጫ ፈላጊዎች›› ነጻ ለማድረግ የሚተገበርም ይሆናል? ለዚህ ውሳኔ ተሳታፊና ተገዢ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF