Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል


ቁጥር 3

 

ከዚህ በፊት ለላክነው ደወል ቁጥር 1 እና 2 እስካሁን ያገኘነው ምላሽ፣ ዝምታም ሆነ ነቀፋ የሚያበረታታ ነው፡፡ ምክንያቱም ዝምታውም ሆነ ነቀፋው አገዛዙ ከዘረጋው የመረጃ ማነቆ አኳያ የሚጠበቅ ነውና፡፡ ስለሆነም ነቀፋውንም እንኳን እንደ ‹‹ነቀፋ›› አንወስደውም - ምክንያቱም እርስዎ አሁን ካሉበት ዓይነት አፋኝ ሥርዓት ቢያንስ የቃል ነቀፋ በመስጠት ታማኝነትን መግለጽ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ይገባናልና፡፡ የልብን ግን ማን ያውቀዋል? እናም እነሆ ደወል 3!   

ስርዓት ሲፈርስ ወሮበላነት ይስፋፋል፡፡ አሁን በተጨባጭ የምናየው ከ‹‹መንግሥት›› የሚጠበቅ አልመስል ብሎናል።ሕግና ስርዓት ያከተመላቸው ይመስላሉ። በተቃራኒው ደግሞ አገራቸውን ለመታደግ ሌት ተቀን የሚደክሙ ዜጎች ኃይልና አቅማቸው አየተጠናከረ ነው።

በአገር መኩራትና መመካት ያስፈልጋል። በኛ እምነት እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኢትዮጵያዊነታችን የምንኮራ ነን። በአገራችንም እንተማመናለን። ምንም ይሁን ምን አገራችን የጋራችን ናት። እናታችንም ናት። አሁን ባሉበት ቦታ ለእርስዎም እናት ናት። ለሚከዱዋትም ለሚያምኑባትም ፣ ቆዳዋን ለሚገፏት፣ ለሚዘርፏት፣ ለከሃዲዎችም ኢትዮጵያ እናት ናት!! በክብር መኖር ለማይመኙ ባንዳዎች የመቀበሪያ፣ የመታሰሪያ፣የመዋረጃ ቦታም አላት።ከዚህ ግን ሁላችንንም ይሰውረን፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ አርፋችሁ ተቀመጡ የተባሉ ብዙሃን ናቸው። ሌሎች ጥቂቶች ግን ኢትዮጵያን እንዳሻችሁ ጋልቡባት፣ ፈንጩባት፣ ዝረፏት፣ ምድሯንም ህዝቧንም ድፈሩ፣ ወዘተ የተባሉ ይመስል ልቅነታቸውን ቀጥለውበታል። የምናየውና የምንሰማው ሁሉ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው። ጥቂቶች ጠግበው ያገሳሉ፤ ብዙሃኑ ግን ለረሃብ፣ ለግርፋት፣ ላስገድዶ መደፈር፣ ለጅምላ ግድያና ለአስከፊ የኑሮ ውድነት ተጋልጠው ይገኛሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ጥቂት የህወሃት ሰዎች ሥልጣን ላይ ስለተቀመጡ ብቻ ሳይሆን እንደ እርስዎ ያለ ተባባሪያቸው በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ለሰብዓዊነት ቅንጣት ግድ ከማይለው አገዛዝ ጋር የሚተባበሩ እንደ እርስዎ ያሉ በመኖራቸው ረሃቡንም፣ ጠኔውንም፣ ስቃየ-መከራውንም፣ መደፈሩንም፣ ሰቆቃውንም ይበልጥ መራራ ያደርገዋል። እስቲ ቆም ብለው ያስቡ!!!

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የቢቢሲው ጋዜጠኛ አንገስ ስቲክለር፣ በማስረጃ አስደግፎ ባስተላለፈው አንገት የሚያስደፋ ሪፖርት በአገራችን ‹‹በመንግሥት›› ደረጃ ስርዓት የፈረሰ፣ ህገወጥነት የነገሰ፣ ወሮበላነት እየተስፋፋ ለመሆኑ ለዓለም በቂ ማስረጃ ነው። የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝን በመደገፍ ወገኖቻቸውን እየረገጡ በሚገኙ ህሊና ቢሶች ላይ እየወረደ ያለው ጥላቻ ከፍቷል። እርስዎስ የዚህ ጥላቻ ሰለባ  መሆን ይፈልጋሉ? ወይስ ከብዙሃኑ ጋር ለፍትህ ይቆማሉ?

“. . . ያለአግባብ ታስሬ ወታደሮች በጅምላ (ስምንት ሆነው) እየተፈራረቁ ሲደፍሩኝ መድማት ጀመርኩ፡፡ ነፍሰ ጡር መሆኔን እያወቁ አስገድደው ሲደፍሩኝና ከወታደሮቹ አንዱ ሆዴን በሰደፍ ሲመታውና በጫማው ሲረግጠኝ የስምንት ወር ፅንስ አስወረደኝ. . . ራሴንም ስቼ ወደቅኩ ስትል የደረሰባትን ለቢቢሲው ዘጋቢ የተናገረችው እህታችን ናት። ብዙዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል። ይህ የስርዓት መፍረስ ምልክት ነው።

አራት የልጅ ልጅ ያዩ ሌላ እናት ደግሞ “. . . ወንድ ልጄን ዓይኔ እያየ ገደሉት። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል እስር ቤት አኖሩኝ። በየእለቱ ጠፍረው በመያዝ አስገድደው ይደፍሩኝ ነበር፡፡ ይህ መከራ የደረሰባቸው ሴት ኦጋዴን ያሉ እናታችን ናቸው። “. . . ተገዶ መደፈር በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ላሉ የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይሆንም ስትል በክልሉ ያሉ ሴቶች ጅምላ ይደፈሩ እንደነበር የተናገችው ሴት ባየችውና በደረሰባት ሁሉ ተስፋ ቆርጣ የሰጠችውን አስተያየት የሰማነው በቢቢሲ አማካይነት ነው። እንደ ‹‹መንግሥት›› መቀጠል የመቅረቱና እንደወሮበላ መኖር የመጀመሩ መገለጫ ከነማስረጃው ከዚህ የተለየ አይደለም። ህዝባዊ የአገር መሪና በዲሲፒሊን የታነጸ ጨዋ የጦር አዛዥ የሌለው ሰራዊት ይዘርፋል፣ ይደፍራል፣ በጅምላ ይጨፈጭፋል። (ጠ/ሚ/ሩ እነዚህን ሁለት ሥልጣኖች ለ20 ዓመታት መያዛቸውን እዚጋ ልብ ይሏል) አቶ መለስና አገዛዛቸው እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። ለዚህም ነው ስርዓት ሲፈርስ ወሮበላነት ይነግሳል ያልነው።

በዚሁ የቢቢሲ ዘገባ መሠረት ለተቃዋሚ ፓርቲ ድምጽ ሰጣችሁ ተብለው በረሃብ የሚጠበሱ ዜጎች ቁጥር ትንሽ አይደለም። በደቡብ ክልል የችግሩ ሰለባ ከሆኑት መካከል ጠኔ ያቃጠላት እናት “. . . ረሃብ በመጽናቱ የቡና ቅጠል እንደ ሻይ እያፈላሁ ከብቶች የሚመገቡትን ሳር ልጆቼን እየመገብኩ ነው ስትል ከመስማት በላይ ምን የሚያሳዝንና አንገት የሚያስደፋ ነገር አለ? በተጻጻሪው ደግሞ ኢህአዴግንና ድቃይ ድርጅቶቹን የመረጡ ጎረቤቶቿን በቅርብ ርቀት እየተመለከተች መራቧን መናገሯ አገራችን በግፍ ጎርፍ መታጠቧን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ሁሉ የሕዝብ ሰቆቃ የአምባሳደር አብድራሺድ ዱላኒ መልስ ‹‹ይህ በመራጩ ሕዝብ የተወገዱ ተቃዋሚዎች ጩኸት ነው፤ ሪፖርቱም ወገናዊ ነው፤ ክሱም መሠረተ ቢስ ነው›› የሚል ነበር፡፡ መልሱ ግራ ያጋባት ጋዜጠኛም ‹‹ግን እነዚህ ሴቶች የተቃዋሚ ደጋፊ ይሁኑ አስገድዶ መድፈርንና ኢሰብዓዊነትን በምንም መልኩ ሲከሰት መቃወም አይገባም ወይ?›› ብላ ነበር መልሳ የጠየቀችው፡፡ በአምባሳደሩ ቦታ እርስዎ ቢሆኑ ምን ብለው ይመልሳሉ? እንደሰው ለኅሊናዎ ይታዘዛሉ? ወይስ እንደ ኢህአዴግ አባልነትዎ ድርጅታዊ መልስ ይሰጣሉ? ሕዝብ ይታዘባል፤ ታሪክም ይመዘግባል፡፡

ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ንጹህ ውሃ ወዘተ ለማግኘት ህወሃት/ኢህአዴግን መደገፍ ዋናው መስፈርት ሆነ። ሥራ ለመቀጠር ለሥርዓቱ ማሸርገድና መታመን መመዘኛ ሆነ። ስብዕናንና ክብርን ለአገዛዙ በማስረከብ በተራ ባዶነት ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳይኖር ተደረገ። “እኛ ይሁንታ ያልሰጠነው፣ እኛ ያልቀባነው፣ እኛ ያልጸለይነው፣ እኛ ያልባረክነውና እኛ ያልመረጥነው በየትም አይሰምርም፣ መኖርም አይችልም” ተብሎ ሃያ አመት ተኖረ!! እርስዎም እንደሸንኮራ ተመጠው በተጣሉት ምትክ በተራዎ ተመጥጠው እስኪጣሉ ለሥርዓቱ ሲጎነበሱ እዚህ ደርሰዋል። ግን እስከመቼ? እስከመቼስ ከግፈኝነት ጎን ይቆማሉ? ዛሬ ወደ ማንነትዎ ለምን አይመለሱም?

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዋል። ትዕቢትና ግፍ ‹‹የአፍሪካ ንጉስ ነኝ›› ይል የነበረውን ጋዳፊን አመድ አድርጎታል። የተቆጣን ህዝብ አልሞ ተኳሽም ሆነ ታንክ እንዲሁም ቅጥረኛ እንደማያቆመው ከሊቢያ፣ ከግብጽና ከቱኒዚያ ህዝብ አመፅ በውል ተረድተናል። ይህ በኢትዮጵያችን እውን የሚሆንበት ቀን እንደሚመጣ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያን ጽኑ እምነት እየሆነ መጥቷል። በዚህ ቀን ምስክር ልንሆንዎ እንወዳለን። ቂም በቀል የሌለበት ህዝብ በሚሰይመውና ዕቅር በሚሰፍንባት እንዲሁም ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነት በሚቀድምባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ በነጻነት ለመኖር አሁኑኑ ይወስኑ
      በሚቀጥሉት የደወል ዕትሞች አገርዎን ማዳን የሚችሉበትንና በኢህአዴግ ውስጥ የጋራ ንቅናቄያችን የሕዋስ አባል ሆነው በመቀጠል በለውጡ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉበትን መንገዶች እያሳወቅንዎ እንሄዳለን፡፡ ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ›› ባለፈ ቂምና በበቀል ሳይሆን በፍትሕና በዕርቅ  ለመመሥረት በሚደረገው ትግል አጋዥ የመሆኛው ቀን ዛሬ ነው፡፡ ጊዜው ካለፈ በኋላ ‹‹እኔኮ ትዕዛዝ ፈጻሚ ነበርኩ›› ለማለት ለተዘጋጁ ሁሉ ግን ይህ የደወል ጥሪ ለእምቢተኛነታቸው በራሱ ማስረጃ ይሆንባቸዋል፡፡      

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF