ደወል
ቁጥር 2
ኢትዮጵያ እንዲህ ትጠይቃለች፡-
“ፍርሃት በፈጠረው የአቅመቢስነት ስሜት ወይም ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ምክንያት በተከሰተ የስሜት መላላትና ደንታቢስነት እስከመቼ መጠቀሚያ ትሆናለህ? እስከመቼስ ለጊዜያዊ ጥቅም ባሪያ በመሆን በአደፈ ኅሊና አንገትህን ደፍተህ ትኖራለህ? ከትላንት ወዲያ የቱኒዚያው ቤን አሊ፣ ትላንት የግብጹ ሙባረክ ዛሬ ደግሞ የሊቢያው ጋዳፊ ታሪክ ሆነዋል፡፡ ነገስ? ነገማ የኔው ጉድ ባለአውራው ፓርቲ መሪ ነዋ!! ስለዚህ ዝናውም፣ ክብሩም፣ ሃብቱም፣ ጊዜም ሁሉም ያልፋል። ስም ግን ከመቃብር በላይ ይውላል፤ አገርም ለዘላለም ትኖራለች፡፡”
በአሁኑ ጊዜ ህወሃት/ኢህአዴግ የገነባው አገዛዝ ስታሊን የሶቪየት ኅብረትን ለሠላሳ ዓመታት፤ ኤንቨር ሆጃ ደግሞ አልባኒያንን ለአርባ ዓመታት ጠፍረው የገዙበት ስልት ነው። በመሆኑም በተገነባው ፓርቲና መንግሥት በሚባለው መካከል ልዩነት አልነበረም፡፡ የስታሊንና ኤንቨር ሆጃ መሰረታዊ የፖለቲካ ማኒፌስቶ የሚያጠነጥነው ዜጎች ፀጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ የማድረግን ስልት በመከተል ነበር። ለቁጥጥር እንዲያመች ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በመዋቅር መያዝ ስለነበረበት ዜጎች አንዱ በሌላው የሰላይ ተሰላይ ተኳኩኖ እርስ በርስ በጥርጣሬ ተፈራርቶ እንዲኖር ተደርጓል።
አሁን ባለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ደግሞ ህወሃት/ኢህአዴግ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የመንግሥት ሰራተኛውን 80%፣ የወጣቱን 90%፣ የገበሬውን 100% እንዲሁም የከተማ ነዋሪውን 50% የኢህአዴግ አባል የማድረግ ዕቅድ ነድፏል፡፡ የዚህ ዕቅድ ኢ-ሰብዓዊ ገፅታ ደግሞ ተግባራዊ የሚሆንበት ስልት ነው።
በመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ሰበብ አዲስ የተቋም አደረጃጀት ተግባራዊ በማድረግ ነባሩ ሰራተኛ በአዲሱ ተቋም ውስጥ ለመመደብና የተሻለ ደረጃ ለማግኘት የኢህአዴግ አባል መሆኑ የውዴታ ግዴታው ነው። ወጣቱ ከትምህርት ተቋማት ተመርቆ አገሩን ለማገልገልና ራሱን ለመጥቀም ዝግጁ መሆኑና ተወዳድሮ ሥራ ለማግኘት ብቃቱ ብቻ ዋስትናው አይደለም፡፡ በመሆኑም በመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ሆነ ህወሃት ባለአክሲዮን በሆነባቸው 90በመቶ በሚሆኑትና መቅጠር በሚችሉት የንግድ ተቋማት በሚወጡ ክፍት የሥራ መደቦች ለመቀጠር ከኮሌጅ ጀምሮ የኢህአዴግ አባል መሆን ይጠበቅበታል።
በገጠር ያለው አርሶአደር ቁራጭ የእርሻ መሬት፣ ከግብርና ባለሙያዎች የምክር እገዛ፣ የማዳበሪያና የዘር ግዢ፣ ብድር ወይም እርዳታ ለማግኘት መወየን ይኖርበታል። የከተማው ነዋሪ ደግሞ ኮንዶሚኒየም ለማግኘት፣ በአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት፣ የአነስተኛ ፕሮጄክቶች ማስፈፀሚያ ብድር ለማግኘት፣ በኑሮ ውድነትና በገበያ ዋጋ መናር ምክንያት በአገዛዙ መስተዳደር መዋቅሮች ተግባራዊ በሚደረጉ የዕርዳታ ዕደላዎችና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ የፍጆታ ዕቃዎች ሽያጭ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን፤ በአጠቃላይ ለመነገጃ የሥራ ቦታ ለማግኘት፣ የመንግሥት ጨረታዎችን ለማሸነፍ፣ የባንክ ብድር ለማግኝት፣ ከጉምሩክ እቃ ለማስለቀቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወዘተ የሥርዓቱ አቀንቃኝና ታዛዥ መሆን ይጠበቅበታል። ይህ ሁሉ እውነታ ደግሞ ፈጽሞ ከእርስዎ የተሰወረ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ምሁር “የተገደሉትን፣ የተራቡትንና የተሰደዱትን ሳይጨምር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሦስት ይከፈላል፡- የታሰሩ፣ በመታሰር ላይ ያሉና ወደፊት የሚታሰሩ” በማለት እንደተናገሩት ለመሆኑ እርስዎ ከየትኛው ይመደባሉ? ይህንን ጥያቄ ሲመልሱ የቤን አሊን፣ የሙባረክንና የጋዳፊን ደጋፊዎች፣ የጥቅም ተካፋዮችንና የፓርቲ አቀንቃኞችን በኅሊና ልብ ይሏል፡፡
ለቁራጭ እንጀራ ራስን አዋርዶ፣ ተገፍትሮ፣ ተደብድቦ፣ የማይበላ ተበልቶ ተገዢነት በተግባር የሚገለጽበት እጅግ አስከፊና በ21ኛው ክፍለዘመን ወደር የማይገኝለት የውርደት አገዛዝ ይህ እርስዎ ያሉበት የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነው። የዚህ ሥርዓት አባል በመሆን ለሚገኝ ትናንሽ ጥቅም ብዙዎች ክብራቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ በየግምገማው በህወሃት ካድሬዎች ስድብን እንደ ምርቃት ተቀበሉ፤ በቆንጆዎቹ እምቢ ባይ ዜጎች ፊት እንደ ወራዶች ተቆጠሩ፤ የህወሃት መኳንንት “ተራሮችን ስላንቀጠቀጠው” ትግላቸው በየጊዜው አዳዲስ ነገር እየጨማመሩበት በመደስኮር አላገጡባቸው። ታዲያ ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል?
ባለፈው ሳምንት በላክነው “ደወል” ቁ.1 ላይ በግልጽ ያስቀመጥነውን በአንክሮ ማንበብዎን እያመሰገንን አሁን ወቅቱ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ” የምትመሠረትበት መሆኑን በድጋሚ ልናሳስብዎት እንወዳለን፡፡ ስለሆነም ከሁሉ አስቀድመው ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ክብርን ይስጡ፤ ለጥቅም ብለው የህወሃት/ኢህአዴግን አባልነት ፎርም በመሙላት ባርነትን አይቀበሉ። በኢህአዴግ ኦርኔል ላይ የውርደት ታሪክዎን በማስፈር በባርነት ለመገዛት፣ በቀጣዩ ትውልድ የመወንጀያና ወደ ወኅኒ የመውረጃ ሰነድ ለራስዎ አያኑሩ::
ከሁሉ አስቀድሞ ማሸነፍ የሚኖርብን በውስጣችን ያለውን ፍርሃት ነው። ለህወሃት/ኢህአዴግ ታማኝ ሊሆኑ የሚችሉት የጦርና የፀጥታ ኃይሎቹ እንዲሁም የስለላ ተቋሙ የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው የጥቂት ዘረኞች ስብስብ በመሆኑ የሕዝብ እምቢተኝነት ሲጠናከር በቀላሉ ይመክናሉ። አመራሮቹ አስተሳሰባቸው በጣም ጠባብ፤ ብቃታቸውም እጅግ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም እነዚህ ኃይሎች ሁሉንም ነገር እንደተቆጣጠሩት አድርጎ ማሰብ ራስን ማዋረድ ነው። ስለዚህም መሸሽ ሳይሆን በየጊዜው ልንፈታተናቸው፣ ልንጎነትላቸውና ልንፋለማቸው ይገባል። ስለሆነም ካሁን በኋላ ሥራው ህወሃት/ኢህአዴግን ከውስጥ ሆኖ የመበታተንና የማፍረስን ሥራ ነው። የነጻነት ኃይሎችም መዋቅራቸውን በማስፋትና በርካታ ህዋሶችን በመፍጠር በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ። የህወሃት/ኢህአዴግን የመዋቅር ስፋት በነፃነት ኃይሎች የመዋቅር ስፋት መጋፈጥ ይቻል ዘንድ ትግሉ ተፋፍሟል፡፡ ህዋሶቻችንን በሁሉም ቦታና ባልተማከለ አደረጃጀት ጭምር በብዛት በመመስረት አገራችን የእኛ መሆኗን ለሕዝባችን የማሳየት ትግሉ ቀጥሏል።
ስለዚህ ፍትሕ፣ ሰላም፣ አንድነትና ዕርቅ የሚሰፍንባትን “አዲሲቷን ኢትዮጵያ” በጥቅም ተደልለው ወይም በፍርሃት ነፃነታቸውን አሳልፈው በሚሰጡ ሰዎች መገንባት አይቻልም። የሕዝብ እግዚኦታ፣ ለቅሶና ምሬት ወደ ተግባር ሲለወጥ የማሳሰቢያ፣ የንሰሃ ወይም የጥሪ ጊዜ አይኖርም፡፡ ከላይ እንደጠቆምነው አሁን እየቀረበ ያለው ጥሪ የኢትዮጵያ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡ ይህንን ጥሪ ንቆ ነገ “እኔኮ ትዕዛዝ ፈጻሚ ነበርኩ” የሚሉ ሁሉ ይህ ጥሪ ራሱ የወንጀላቸው ማስረጃ ሆኖ እንደሚቀርብባቸው መገንዘብ አዋቂነት ነውና ይህንን እየራደ የሚገኝ ሥርዓት “እንቢ!” ያሉ ወገኖቻችን የሚኖራቸውን ሞገስና ክብር፤ ከማይቀረው የኢህአዴግ ውድቀት በኋላ ተባባሪዎቹ ላይ ከሚደርስባቸው ውርደት ጋር በማነጻጸር ዛሬ ለእውነት እንቁም፡፡ ወደ ልባችን እንመለስ!! ለጥሪውም ምላሽ እንስጥ!!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡